የሦስተኛው ሲኒማ ቀዳሚት አቀንቃኝ በኢትዮጵያ በሆነችው ቅድስት ይልማ የፊልም ስራዎች እና በተለይም በ'ዶቃ' ፊልም ዙሪያ የተደረገ ዳሰሳ።
የዓለምን የሲኒማ እንቅስቃሴ ተፈጥሮ እና አላማውን በመፈተሽ በሶስት የመክፈል ዝንባሌ በፊልም ሰሪዎች እና ተመራማሪዎች ዘንድ በእጅጉ ይዘወተራል፤ አንደኛው ሲኒማ፣ ሁለተኛው ሲኒማ እንዲሁም ሶስተኛው ሲኒማ በማለት፡፡ እንደስያሜያቸው ሁሉ ፍጥረታቸውም በተዋረድ ነው፤ የመጀመርያው ሲኒማ ፈጣሪዎቹን በእጅጉ ይመስላል፤ የሲኒማቶግራፍ ቴክኒክ በቢዝነስ እና ፈጠራ ባለሞያዎቹ የሉምየር ወንድማማቾች አማካኝነት በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ከተዋወቀ እና ከፍተኛ የህዝብ ተቀባይነት ካገኘ ወዲህ በምዕራቡ አለም በተለይ የሆሊውድ ፊልም ስቱድዮዎች ጥበብን ኢንደስትሪያላይዝ የማድረግ አዝማምያ በእጅጉ ተስተውሏል፡፡ የመጀመርያው ሲኒማ እንደሌሎች ሳሙና እና መሰል የኢንደስትሪ ምርቶች በከፍተኛ ቁጥጥር የሚከወን፣ ረጅም የስልጣን ተዋረድ ያለው እና ከፍተኛ መዋለ ነዋይ የሚፈስበት የመዝናኛ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ለአዳዲስ ፈጠራዎች እና ባለሙያዎች በሩ ዝግ መሆኑ፣ እውስጡ ያሉትንም ጠቢባን ከዘልማዳዊ የሲኒማ ቴክኒኮች ፈቅ እንዳይሉ እግር ተወርች ማሰሩ አይነተኛ መለያዎቹ ናቸው፡፡ ፈርስት ሲኒማ ምንም እንኳ ዘልማዳዊ እና ተቸካይ በምርቱም ቢሆን አልፎ አልፎ ብቅ ከሚሉ ዘመን አይሽሬ ውጤቶቹ በቀር በአብዛናኛው የአይን ከረሜላ የአዕምሮ ላንቲካ ከፍ ሲልም የፕሮፖጋንዳ ማሽን፣ የኢድዮሎጂ ስሪንጅ በመሆኑ ቢወቀስም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሰረቱን እያፀና እና ገቢውን እየጨመረ የአለማችን ትልቁ ኢምፓየር ለመሆን በቅቷል፡፡
ሁለተኛው የአውሮፓ አርት ሀውስ ሲኒማ እንደሌሎቹ የአቫንትጋርዲዝም የስነ-ጥበብ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ዘልማድ ላይ የሚደረግ አመፅን መሰረት ያደርጋል፡፡ በተለይም የቀዳሚው ሲኒማን ዶግማቲክ አካሄድ እና የደቦ ፈጠራን በመቃወም ሸራው የሰዓሊው የምናብ ውጤት እንደሆነው ሁሉ አቡጀዴው ላይ የሚታየው የብርሀን ትእይንትም በአዘጋጁ መሪነት ኦርከስትሬት የሚደረግ ሲንፈኒ ነው የሚል መከራከሪያን ይዟል፡፡ ሰከንድ ሲኒማ በውስጡ የተለያዩ ሰብ-ዣንራስ ያሉት ሲሆን የፈረንሳይ ኒው ዌቭ እንቅስቃሴ፣ የጣልያን ኒኦሪያሊዝም፣ የሱርያሊዝም እንቅስቃሴ እና ፖኤቲክ ሲኒማ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሶስተኛው ሲኒማ ከተቀዳሚው እና ተከታይ የሲኒማ አይነቶች በእጅጉ ይለያል፡፡ ከድህረ ቅኝ ግዛት ወዲህ በላቲን አሜሪካ፣ አፍሪካ እና ኤዥያ ሀገራት በስፋት የታየው ይህ እንቅስቃሴ በአርጀንቲናውያን የፊልም ባለሙያዎች ፈርናንዶ ሶላንስ እና ኦክታቪዮ ጌቲኖ በ1969 እ.አ.አ “Towards a Third Cinema” የሚል ማኒፌስቶ ከፃፉ ወዲህ ሲኒማን ለፖለቲካ ትግል እና ማህበረሰባዊ ለውጥ የመጠቀም አዝማሚያ በእጅጉ ተስፋፍቷል፡፡ ፈርናንዶ እና ኦክታቪዮ ፈርስት ሲኒማን የቀኝ ገዢዎችን እሴት ለየዋህ ተመልካች የሚግት እና የበታችነቱን በፀጋ እንዲቀበል የሚያስገድድ ብለው ሲተቹት ሰከንድ ሲኒማን ደግሞ ተመልካች ግለኝነት እንዲሰማው እና ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን ቁርኝት (collective identity) በመስበር ህዝቦች ለጋራ አላማ አና ነፃነት እንዳይታገሉ ያደርጋል በማለት ይነቅፋሉ፡፡ የጀርመኑ ፀሐፊ ተውኔት በርቶልት ብሬሽት “Art is not a mirror held up to reality but a hammer with which to shape it.” እንዲል እነ ፈርናንዶም ካሜራ የህዝቦች ትግል ጦር መሳሪያ መሆኑን እና ጥይቱም በሰከንድ ሀያ አራት ጊዜ የሚተፋው ምስል እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአለም የፀረ-ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ እና ትግል ላይ የትዕምርትነት (Symbol) ድርሻ እንዳላት ሁሉ በዚህ ትግል ውስጥ ሲኒማን እንደ አይነተኛ መሳርያ በመጠቀም እንቅስቃሴ ውስጥም አጋፋሪ የሆኑ ሁለት ጉምቱ የንድፈ ሀሳብ እና ተግባር ባለሙያዎችን ለዓለም አበርክታለች፡፡ እነሱም ፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ እንዲሁም ፕሮፌሰር ተሾመ ሀብተ ገብርኤል ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የፕሮፌሰር ሀይሌ ስራዎች ለምሳሌ እንደ “ምርት ሶስት ሺህ አመት”፣“Imperfect journey”, “ጤዛ”፣ “Sankofa” ያሉት በዋነኝነት የፖለቲካል ይዘት ሲኖራቸው በውስጣቸውም የድህረ-ቅኝ ግዛት ጉዳዮች፣ የባህል እና ስልጣኔ ቁርሾ፣ የሀገር እና ተውልድ እጣ ፈንታ፣ የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት እና ሴራ እንዲሁም መሰል ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናሉ፤ በዚህም በአለም ጉምቱ የሶስተኛው ሲኒማ ፊልም ሰሪዎች ረድፍ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ፕሮፌሰር ሀብተ ገብርኤል በአለም እንጂ በኢትዮጵያውን ዘንድ እምብዛም የማይታወቁ፣ በሎስ አንጀለስ UCLA, School of Theatre Arts, Film and Television ውስጥ በፕሮፌሰር ማዕረግ ያገለግሉ የነበሩ ሲሆን በዘርፉ በርካታ የምርምር ወረቀቶችን እንዲሁም “Third Cinema in the Third World” በሚል ርዕስ ጠለቅ ያለ ኦውቶሪቴቲቭ አካዳሚያዊ መፅሐፍ ለአለም አበርክተዋል፡፡
የአለምን የሲኒማ እንቅስቃሴ በሶስት ከፍለን በጥቂቱ ለመዳሰስ ሞክረናል፤ ወደ ሀገራችን መለስ ብለን የእውቅ እና ተወዳጅዋን የፊልም አዘጋጅ ቅድስት ይልማን ስራዎች ብንመለከት በአመዛኙ በሶስተኛው ሲኒማ ስፔክተረም ውስጥ የምናገኛቸው ይሆናል፡፡ በርግጥ የቅድስት ፊልሞች በተመልካች ዘንድ ያላቸውን ከፍተኛ ተቀባይነት እና አንፃራዊ ፋይናንሻል ሰክሰስ እንዲሁም የስራዎቿን ከፍ ያለ ኪነ-ጥበባዊ ለዛ አልዘነጋንም፡፡ ነገር ግን የስራዎቿን ተደጋጋሚ ጭብጣዊ ይዘት እንዲሁም አርቲስቲክ ቮይስ እና ኦቶሪያል ኢንቴንት ከተመለከተ ከላይ ያነሳናቸው የሶስተኛው ሲኒማ አላማ እና ባህሪያት ጋር ትይዩ ሆነው ማግኘታችን አይቀርም፡፡ ከቅድስት ፊልሞች መካከል በተለይ ረቡኒ፣ እረኛዬ፣ ታዛ እና አሁን ደግሞ ዶቃ የሚሰኙት ፊልሞቿ በከፍተኛ ሁኔታ ህብረተሰባዊ ጭብጦች የሚንፀባረቅባቸው፤ እንደ ባህል፣ መሬት፣ ኢኮኖሚ፣ አስተዳደር፣ እውቀት፣ ስልጣኔ፣ ተፈጥሮ፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ማንነት፣ ፆታ፣ የእርስ በእርስ ግጭት፣ ጥቅመኝነት እና መስዕዋትነት ላይ የሚያጠነጥኑ ሲሆኑ አላማቸውም በዋነኝነት መግለጥ፣ መጠቆም፣ መተርጎም፣ ማስጠንቀቅ፣ መገሰፅ እና መተንበይ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ ቀጥሎ እነዚህ አብይ ጭብጦች ከልዩ ልዩ የሲኒማ ቴክኒኮች ጋር ተዛንቀው ዶቃ በተሰኘው የአዘጋጅዋ አዲስ ፊልም ላይ እንደቀረቡ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡
በአጠቃላይ ርዝማኔው አንድ ሰዓት ከሃምሳ ገደማ የሚፈጀው ዶቃ ፊልም ዘውጉ ዲስቶጵያን ፊክሽን የምንለውን አይነት ይመስላል፡- ይህ ዣንራ በዋነኝነት ስለወደፊቱ የሰው ልጅ አስከፊ እጣ ፈንታ የሚተነብይ ሲሆን እንደምክንያትነትም በአብዛኛው አምባገነነናዊ እና በሙስና የተጨማለቀን አስተዳደር፣ ስርዓት አልበኝነትን እና ዘመነ መሳፍንታዊ አገዛዝን፣ የቴክኖሎጂ ከቁጥጥር ውጪ መሆንን አልያም ተፈጥሮአዊ አደጋን በመንተራስ ሊፈጠሩ የሚችሉ ማህበረሰባዊ መናጋቶችን እና አስከፊ የኑሮ ሁኔታን የሚያሳይ የሲኒማ አይነት ነው፡፡ በርግጥ ይህንን ስንል አንድ የሙግት ጫፍ ተያይዞ ሊነሳ ይችላል፤ እሱም የእውነት ዶቃ ዲስቶጵያን ፊክሽን ነው ወይ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በዲስቶጵያን ፊክሽንነቱ ከተስማማን ሲኒማው እያስጠነቀቀን ያለው በጀመርነው መንገድ አቅጣጫ አይቀሬ መዳረሻችንን በመጠቆም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን already በዶቃ መቼት እና በአሁኗ ኢትዮጵያ መካከል እምብዛም ልዩነት የለም፤ ፊልሙ ነገን ከመጠቆም ይልቅ ዛሬን የሚገልጥ ነው የሚል ሙግት ቢመጣ እምብዛም ለመቃረን ያስቸግራል፡፡
ያም ሆነ ይህ፤ የዶቃ world of story ከቀጥተኛ ውክልና ይልቅ ይሁነኝ ተብሎ ሜታፎራይዝ እንደተደረገ ግልፅ ነው፡፡ ባዝንን፣ ሞራን እና ቀኝ ሞራን በትክክል እዚህ አካባቢ ናቸው ብሎ ለመጠቆም ቢቸግረንም ስናያቸው አንዳች አይነት እንግዳ ትውስታ (Deja vu) ይሰማናል፡፡ የቅድስትን ፊልሞች ደጋግሞ ለተመለከተ ታዳሚ ቅድስት ከሜታፎር እና ትዕምርት ጋር ያላትን ቁርኝት ልብ ሳይለው አይቀርም፡፡ እዚህ ጋር ሞራ እና ቀኝ ሞራ የሚሉ የአካባቢ መጠሪያዎች ከሜታፈርነትም አልፈው በሊትራላይዜሽን አገባባቸው ስላቅን ይጋብዛሉ፤ በግራም ይሁን ቀኝ ሞራ ሞራ ነው፤ አይንን ይጋርዳል፡፡ እንዲህ አይነቱ ስላቅ በገፀ-ባህሪያቱ እንግዳ ስም አሰጣጥ ውስጥም እንመለከተዋለን፤ ላካን፣ ጋሩድ፣ ቶማክ፣ ቴንጎ፣ ሳሳ፣ አባሼ የመሳሰሉት ስም አሰጣጦች ሁለት መልክ ያላቸው ይመስላል፤ አንድም የሚታወቀውን እንግዳ የማድረግ ፍላጎት (Defamiliarization) እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ስላቅን የመጋበዝ (Ridicule የማድረግ) ዘዴ ይመስላል፡፡ እንዲህ አይነቱ ስላቅ በገፀ-ባህሪያቱ ፀጉር ቁርጥም ላይ ይስተዋላል፤ የገፀ-ባህሪያቱ ፀጉር ቁርጥ ስታይል አንድም ለታሪኩ መቼት እና ድባብ ተዓማኒነት ሲጨምርለት በሌላ በኩል ደግሞ የሁለቱ ሰፈርተኞች ዋና እና ብቸኛ የሚታይ ልዩነት ሆኖ ቀርቧል ፤ እነዚህ ከፀጉር ቁርጣቸው በቀር እዚህ ግባ የሚባል ልዩነት የሌላቸው ቡድኖች Arbitrarily ሞራ እና ቀኝ ሞራ በመባባል፣ በሙስና እና ሴራ በተጨማለቀ አስተዳደር እና ከጀርባ በሚጋልቧቸው ስውር እጆች ሲጠፋፉ እንመለከታለን፡፡
ይህን ታሪክ ለመተረክ ከገፀ-ባህሪያቱ ፐርስፔክቲቭ ይልቅ ካሜራው እንዲተርከው ተመርጧል፤ ይህም ማለት ግለሰባዊ ስሜት (Subjectivity) ከተጫነው ምልከታ ይልቅ ጉዳዩን Objectively እንድንመለከተው እና በስሜት ከመዋጥ (Sentimental Identification) ይልቅ የነገሩን እውነታ በምልዓት እንድንረዳው ያስችላል፡፡ ካሜራው ሁሉን አወቅ (omniscient) እና ሁሉም ቦታ የሚገኝ (omnipresent) በመሆኑ ከአብዛኞቹ ገፀ-ባህሪያት ይልቅ ተመልካቹ ለጉዳዩ የተሻለ ግንዛቤ አለው፡፡
የገፀ-ባህሪያቱን ግንዛቤ ያየን እንደሆነ የፕሌቶ የዋሻው ስር ተረት (Allegory of the cave) ትዝ ይለናል፤ እንደ ፕሌቶ የዋሻው ውስጥ ገፀ-ባህሪያት ሁሉ የዶቃም ገፀ-ባህሪያት እዛው ዋሻ ውስጥ ተወልደው ያደጉ፤ ከዋሻው ውጭ ስላለው ሰፊ አለም ግንዛቤ የሌላቸው ይልቁንም ከውጭ እየገባ ግድግዳው ላይ የሚያርፈውን ጥላ እንደ እውነታ ተቀብለው እየተመሰጡ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ይመስላሉ፤ አያውቁም አለማወቃቸውንም አያውቁም፤ አናውቅም አለማወቃችንንም አናውቅም፡፡ ለዚህም ይመسላል ካሜራው ከውጭ ወደዋሻው ውስጥ እንደተመለሰ እንግዳ ድንቁርናቸውን እንድንታዘብ የሚጋብዘን፡፡ የሲኒማቶግራፊ ቴክኒክን እና ኤዲቲንግን በተመለከተ በአብዛኛው እውናዊነትን እና የምስል ተፈጥሯዊ ተከታታይነትን (Natural continuity) የተከተለ ከአንዳንድ ቪዥዋል ኢፌክቶች በቀር እምብዛም ለራሱ ትኩረትን የሚስብ Cinematic technique ባለመኖሩ ተመልካች ትኩረቱ ሳይናጠብ እና እምነቱ ሳይስተጓጎል ለርዕሰ ጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲመለከት አስችሎታል ማለት ይቻላል፡፡
ሌላኛው ልብ ሳይባል የማይታለፍ ጉዳይ ቢኖር ቦታን እንደ አንድ ገፀ-ባህሪ (Setting as a character) የመጠቀም እና ድባብን በከለር እና ቶን በጠቅላላው በቪዥዋል ሉክ የተገለፀበትን መንገድ ነው፡፡ የዶቃ ፊልም ታሪክ በዋናነት በሁለት መቼቶች የተዋቀረ ሲሆን አንደኛው በባዝን ከተማ እና አካባቢዋ የሚያጠነጥን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከቦምብ ፍንዳታው በኋላ ማሪስ በህይወት ተርፋ ትምህርት ቤት ውስጥ ለእድሜ እኩዮቿ የሰላም እና መልካም ምኞት ንግግር ስታደርግ ነው፡፡
ይህ ሲኩኤንስ መጀመርያ እና መጨረሻ ላይ በመምጣት ታሪኩን ቡክኤንድ የማድረግ ድርሻ ሲኖረው የባዝን ፕሎት ላይን ደግሞ ማሪስ አይኗን ለቅፅበት ጨፍና እስክትገልጥ ድረስ ያሉትን ሰከንዶች በመለጠጥ በአእምሮዋ ያለውን ትውስታ መለስ ብለን የቃኘንበት ነው፡፡ በርግጥ ይሄ ትንታኔ የማያስኬድባቸው ምክንያቶች አሉ፤ በዋናነት የካሜራው ሁሉን አወቅ እና ተገንጣይ መሆን ማርየስ ያልነበረችባቸውን እና የማታውቃቸውን ጉዳዮች ሁሉ የሚያስቃኘን በመሆኑ የባዝን ሲኩኤንስ ሙሉ ለሙሉ የማሪስ ፐርስፔክቲቭ ነው ብሎ ለመቀበል ይቸግራል፡፡
ያም ሆነ ይህ፤ በሁለቱ አብይ ሲኩኤንሶች መካከል ግልጥ የሆነ የድባብ እና ቪዥዋል ሉክ ልዩነት እንዳለ እንታዘባለን፡፡ ባዝን ከዛም ከፍ ሲል ደግሞ ሞራ እና ቀኛሞራ የሚባሉት መንደሮች ስንመለከት ሜዳማ እና በረሃማ የሆነ፤ አረንጓዴ ቅጠል የማይታይባቸው፤ ዛፎች የሞቱበት፣ ሳሮች የደረቁበት፣ አዋራ እና ፀሐይ የሚሰለጥኑበት፣ አንዳንዴም በጭስ የታፈነ፣ አልፎ አልፎ የምናያቸው ከብቶችም አጥንታቸው የደረቀ ቆዳቸው የተጣበቀ… በመልክም ቢሆን የበረሀ አሸዋ ቀለም የሚመስል ወደ ቢጫ እና ብርቱካናማ ያደላ ሉክ የያዘ ነው፡፡ እዚህ በአካባቢው ያለ ስር የሰደደ ጥላቻ እና ክፋት ተፈጥሮንም እንደ ካንሰር አመንምኖ የገደላት ይመስላል፣ እንደ ቀዬው ጀማ ሁሉ ተፈጥሮም ሰው ጠል (Hostile) ሁናለች፡፡ በአጠቃላይ የአካባቢው ገፅታ፣ መልክ እና የገፀባህሪያቱን ሁኔታ ስንመለከት ሌላኛውን ታዋቂ ዲስቶጵያን ፊልም ማድ ማክስ ፊዩሪ ሮድን ያስታውሰናል፡፡
በሌላ በኩል የማርየስ የትምህርት ቤት ሲኩኤንስ፤ ከመጣንበት የባዝን ከተማ አንጻር ሌላ ፕላኔት ላይ ያለ ይመስላል፤ እዚህ ተፈጥሮ ትተነፍሳለች፣ የህፃናቱ ፊት ላይ ተስፋ ይነበባል፣ አካባቢውም በተለያዩ ደማቅ ቀለማት ያጌጠ ነው፤ እንደማርየስ ንግግር ሁሉ የመቼቱ እይታዊ አላባዊያኖችም ተስፋን ያበስራሉ፤ የተሻለ ሁኔታን ያስናፍቃሉ፡፡ ይህንን በማሳካት እና የሲኒማን ቪዥዋል አቅም በማሳየት ረገድ በፕሮዳክሽን ዲዛይን፣ እና ከለር ግሬዲንግ የተሰራውን ስራ ሳናደንቅ አናልፍም፡፡
ዶቃ ፈርጀ ብዙ ነው፤ ከዚህም በላይ ሊተነተኑ እርስ በእርስ ሊያያዙ የሚችሉ ኢለመንቶችን በውስጡ አጭቋል፤ ለምሳሌ ያህል እሳትን ከርዕስ ግራፊክሱ ጀምሮ እስከመጨረሻው ፍንዳታ ድረስ እየደጋገመ እንደ ሌት ሞቲፍ የማምጣቱን ነገር፣ እሳት እና ዘረኝነት ያላቸውን ሜታፎሪካል ግንኙነት፤ የትውልድ እዳ መዋረስን የአባሼ እና ላካን የባህሪ እና ፍላጎት መመሳሰል እንዲሁም የነሱ እዳ ለማሪስም ወይም እሷ ለወከለችው አዲሱ ትውልድ እዳ እና ጠባሳ ሆኖ መሻገሩ፤ እዚህ ግባ የማይባሉ አብዘርድ ምክንያቶች የሚያስከትሉትን ዘላለማዊ ስቃይ፤ የላካን ባለ ዲግሪ የተማረ ሆኖ መሀይምነት፤ የመምህርት ስኒን እና እሷ የወከለቻቸው ምሁራን ማህበረሰብ በፍርሀት ቆፈን በር ዘግቶ መማቀቅ፤ የማሪስ ከእናቷ ተነጥላ መጥፋት እና በአባቶቹ ዳፋ አቅጣጫ ከጠፋው ማንነቱን ለማግኘት ከሚባዝን አዲሱ ትውልድ ጋር ያላት ግንኙነት፤ በተለይ ከዚህ ሁሉ ቁርሾ እና ጭፍጨፋ ጀርባ ያሉት መልካቸው ጭምር በደንብ እንዳይታዩ የተደረጉት ነገር ግን በስውር እጃቸው ሲዘውሩት የምንመለከተው ማስተር ማይንዶች መጨረሻ ላይ የሚገባቸውን ፖይቲክ ጀስቲስ ያለማግኘታቸውን እና ከነ መኖራቸውም ያለመታወቃቸው ጉዳይ፤ እኛም የችግራችንን ምንጭ ፈልፍለን ካለማግኘታችን እና ካለንበት የአዙሪት ጉዞ ጋር አገናኝተን ብንወያይበት ዶቃ ፊልም እንደ ቱባ ክር እየተተረተረ የሚሄድ ሰፊ ትርጉም ሊሰጠው የሚችል ስራ እንደሆነ እንረዳለን፡፡
በስኮር አጠቃቀምም ረገድ እጅግ የሚደነቅ ሙከራዎችን ያየንበት፤ እንደ ዋሽንት፣ ከበሮ፣ ክራር እና መሰንቆ ያሉ ሀገር በቀል የሙዚቃ መሳሪያዎች ሲኒማን ለማጀብ የሚያስችል አቅም እንዳላቸው፣ ባለሙያ ካገኙ የስሜት ዳይናሚዝምን መሸከም እንደሚችሉ ዳግም በመሳጭ ሁኔታ የተመለከትንበት ነው ማለት ይቻላል፡፡
በመጨረሻም፤ ምንም እንኳ ማህበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ መሻሻል ወይም ለውጥ ለማምጣት የሲኒማ ጉልበት እና ተፈጥሮ እጅግ የተመቸ ቢሆንም በሀገራችን ኢትዮጵያ የሰርድ ሲኒማ እንቅስቃሴ እምብዛም የፊልም ሰሪውን ትኩረት የሳበ አይመስልም፡፡ በርግጥ ሲኒማን በሶስት በኩል ገንዘብ፣ ጥበብ እና ቴክኖሎጂ የሚጓተቱት ሚድየም በመሆኑ በዚህ መሀል አካሄዱን መምራት እና ለተሻለች ኢትዮጵያ መፈጠር የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ማመቻቸት ቀላል ስራ አይደለም፡፡ ነገር ግን እንደ ቅድስት ይልማ ያሉ በፊልም ሙያ ለሀገራቸው መሻሻል የሚችሉትን ለማድረግ የሚጥሩ ፊልም ሰሪዎችን ስራ ማጥናት፣ እውቅና መስጠት እና ማበረታታት ሌሎችም ነባር እና አዳዲስ ፊልም ሰሪዎች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችል ይመስለናል፡፡
ነሐሴ/ 11/ 2016
← Back to Doka